በመጀመሪያው ምድብ ማለትም ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ተወስኗል።
በ2ኛ ምድብ ጥቅምት 16 ቀን 2013 ደግሞ በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ነው የተወሰነው።
በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ መወሰኑ ነው የተገለጸው።
በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተገኝተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው ውይይት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ሚኒስትሮችም ተገኝተዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት ስለቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ገለፃ አድርገዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ከሁሉም ክልሎች የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ውይይት መካሄዱንና የውሳኔ ሃሳብም መቅረቡን አንስተዋል።
የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አስመልክቶም ሁሉም ተፈታኞች ለፈተና እንዲቀመጡ የሚል ውሳኔ መተላለፉ ተገልጿል።
የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሕዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው።
በተመሳሳይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀቁና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥም መወሰኑ ተጠቅሷል።
የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚወጣው መመዘኛ በግል ትምህርት ቤቶችም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
የግል ትምህርት ቤቶች የምዝገባ ክፍያ በ2012 ዓ.ም በነበረው መጠንና የክፍያ ስርዓት መሆን እንዳለበትም ተገልጿል።